በዓለ ስቅለት እና በዓለ እግዝእትነ ሲገጣጠሙ ይሰገዳል ወይስ አይሰገድም?

IMG_1421ምንም እንኳ ይህ ጥያቄ በብዙ ሰዎች ዘንድ የተመለሰ ቢሆንም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መምጣታቸው ሁለት ነገሮችን ስላመለከተኝ እኔም እንደገና በአጭሩ ለመመለስ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው የተሰጠው መልስ ለሁሉም እኩል አለመድረሱ ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ አንዳንዶቻችንም ተደጋሞ አንድ ዓይነት መልስ በማየት የማረጋገጥ ፍላጎት ያለን ይመስላል፡፡
ይህን የመሰሉ ተደጋጋሚ ጥቄዎች ሲገጥሙን ነገሩን ማየት ያለብን ከመሠረታዊው የቤተ ክርስቲያን ትውፊትና አስተምህሮ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ይህ ጥያቄ የበዓሉን አከባበር የሚመለከት ስለሆነ በቤተ ክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖናም ሆነ ትውፊት መሠረት በዓላት የሚበላለጡ ከሆነ የሚበልጠው የትኛው ነው ከሚለው ቀላል ጥያቄ ልንነሣ እንችላለን፡፡ በዚሁ መሠረት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዙት የጌታችን ዐበይት በዓላት ቀጥሎም የጌታችን ንዑሳት በዓላት መሆናቸውን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡
ከሚውሉበት ዕለት አንጻር ካየን ከጌታችን ዘጠኙ ዐበይት በዓላት ውስጥ አምስቱ ዐዋድያት በዓላት (Movable feasts) ስለሆኑ ዕለት ይጠብቃሉ፡፡ እነዚህም ሆሣዕና፣ ትንሣኤ እና ጰራቅሊጦስ እሑድን ሳይለቁ ሲውሉ ስቅለት ዐርብን ዕርገት ደግሞ ሐሙስን ባለመልቀቅ ይውላሉ፡፡ የቀሩት አራቱ ማለትም ጽንሰት ወይም ትስብእት፣ ልደት ፣ ጥምቀትና ደብረታቦር ደግሞ ዐዋድያት ስላልሆኑ (Immovable) ወርና ቀን ሳይለዋውጡ በተለያዩ ዕለታት ይውላሉ፡፡
አሁንም ግን ከእነዚህ ከዘጠኙ ደግሞ ዐራቱ እጅግ የተለየ ክብር አላቸው፡፡ እነዚህም ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለትና ትንሣኤ ናቸው፡፡ ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ታላላቅ የደስታ በዓላት ስለሆኑ ደስታው መብልና መጠጥን በማካተትና ሌሊት በመቀደስ የሚከበሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ታላቅነታቸው የተነሣም ሦስቱም የዐርብንና የረቡዕን ጾሞች ሳይቀር የመሻር ሥልጣን አላቸው፡፡ ልደትና ጥምቀት ዐርብና ረቡዕ ቢውሉ ይበላሉ፡፡ ትንሣኤ ምንም እሑድን ባይለቅም በሚቀጥሉት 50 ቀናት ውስጥ ያሉትን ረቡዕ እና ዐርብ በሙሉ ያሽራቸዋል፡፡ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ትውፊት ደግሞ ከልደት ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ባለው የዘመነ አስተርእዮ ጊዜ ውስጥ ያሉትም ረቡዕ እና ዐርብ ቀናት በሙሉ በልደቱና በጥምቀቱ (በአስተርእዮው) ታላቅነት ይሻራሉ፡፡ ከዚህም በላይ በትክክል ቀኖናውንና ትውፊቱን ጠብቀን የምናከብር ቢሆን በእነዚህ ዕለታት ሰው ቢሞት አይለቀስም፤ በአንጻሩ ሰርግና ሌላ ሥጋዊ ተድላ ደስታ ማድረግም የተከለከለ ነው፡፡ በዓላተ ቅዱሳን ቢገጥምም ማዘከር ይደረግለታል እንጂ በዐቢይነት የሚከበረው የጌታችን በዓል ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት በዓለ ትንሣኤው የሚውለው የዐቢይ ሰማዕት የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ዕረፍት ዕለት ሚያዚያ 23 ቀን ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ዕለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ወጥቶ እንደሌላው ጊዜ ንግሥ ተደርጎ ሊከበር አይችልም፡፡ ይህም ስለማማያመች ብቻ ሳይሆን ስለማይገባም ነው፡፡ በመሆኑም በዓሉ ከትንሣኤ በኋላ ባሉት ቀናት በአንዱ ይከበራል እንጂ የትንሣኤ ዕለት የሚከበረው የጌታችን የትንሣኤው በዓል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ በዓላት ማንኛውን ጾምንም ፣ ሐዘንንም ደስታንም ይሽራሉ ማለት ነው፡፡
ልክ እንደነዚህ ደግሞ በዓለ ስቅለት ዐርብን ሳይለቅ ቢውልም ይህም ከዐቢይነቱ የተነሣ እንደ ቀደሙት እንደ ሦስቱ ራሱን ችሎ የሚሽራቸው ነገሮች አሉት፡፡ እንዚያ ጾምን እንደሚሽሩት ስቅለት ደግሞ በምንም ምክንያት ጾም ተጹሞባት የማያውቀውንና ከዐሥርቱ ትእዛዛት አንዷ የሆነችውን ቀዳሚት ሰንበትን ሽሮ ከሰንበትነት አውጥቶ የራሱን ጾምነት አውርሶ ያስጾማታል፤ ስሟንም አስለውጦ ቀዳሚት ስዑር (የተሻረች ሰንበት) አስኝቶ ያስገብራታል፡፡ ስለዚህ ስቅለት በፍትሐ ነገሥቱ የበዓላት ክብር ቅደም ተከተል መሠረት ከጌታችን ዓበይት በዓላት ቀጥላ የምትከበረውን ሰንበትን ከሻረ የማይሽረው ሌላ ምንም በዓል ሊኖረው አይችልም ማለት ነው፡፡ የቀደሙት ሦስቱ ከታላቅነታቸውና ከታሪካዊ ዳራቸው የተነሣ ሌሊት እንደሚቀደሱት ስቅለት ደግሞ በተቃራኒው ምንም ቀን ቢገጥመው ቅዳሴ አይቀደስበትም፡፡ ለምሳሌ የዚህ ዓመት ስቅለት የእመቤታችን ወርኃዊ በዓል ጋር ስለገጠመ ይቀደስ አይባልም፤ የሚከበረው በሚበልጠው በጌታችን በዓል ስለሆነ፡፡ እንኳን በወርኃዊ የእመቤታችን በዓል ቀርቶ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ከሆነውና መጋቢት 29 ቀን ከሚከበረው ከትስብእት ጋር ቢደረብ እንኳ በዓሉ ትስብእትን አስቀድሞ በቅዳሴ አይከበርም፤ ይልቁንም ስቅለትን አስበልጦ በጾም በሰጊድ ይከበራል እንጅ፡፡ ስለዚህ ስቅለት ከዘጠኙ ዓበይት በዓላትም እንደ ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ሌላውን ይሽራል እንጂ በሌላ በዓል አይሻርም፡፡ እንኳን ራሱን ሊያስደፍር ሰንበትንም ሽሯልና ፡፡
እንኳን በዓለ ስቅለት ሰሙነ ሕማማትም እነዚህን በዓላት ይሽራቸዋል፡፡ ሆኖም ከሰሙነ ሕማማት ሐሙስ በቅዳሴ ትሻራለች፡፡ ይህም እንኳ ራሱ ጌታ ሐዲሱን ሥርዓት ስለመሠረተበት ቢሆንም ስግደቱና ሌላው ሥርዓት በሙሉ በሕማማቱ ሥርዓት የሚሔድ ስለሆነ እንደተሻረ የሚቆጠር አይደለም፡፡ ልክ ቀደም ብለን ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ሐዘንን ይሽራሉ እንዳልነው ስቅለትም ማንኛውንም ደስታ ትሽራለች፤ ዕለቱ የሐዘን (ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን፣ መከራ መስቀሉን በማሰብ)፣ በለቅሶ፣ በጾም በስግደት የሚከበር ስለሆነ የሌላ በዓል ጠባይን በፍጹም ሊወርስ አይችልም፡፡ እንደ ትውፊታችንማ ቢሆን እንኳን የራሱ የስቅለት ዕለት የሚውል በዓል ቀርቶ በዐቢይ ጾም የሚውሉ ዐመታዊ በዓላት እንኳ በንግሥ፣ በማኅሌትና በከበሮ በሌላ ወቅት እንዲከበሩ ነበር የተወሰነው፡፡ ምክንያቱም ልክ በዓለ ሃምሳን እንደ አንዲት ዕለተ ሰንበት ቆጥረን እደምናከብረው ዐቢይ ጾምም እንደ አንድ ዕለት ጾም በአንድ ሥርዓት ብቻ እንዲጾም የተወሰነ ነው፡፡
በጥንቱ ዐለም አቀፍ ሥርዓትና ትውፊት ከሆነ በዐቢይ ጾም ፈጽሞ ቅዳሴም አይቀደስም ነበረ፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ጌታ አርባውን ቀን እንደ አንድ ቀን ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋም ሳይጥፍ ስለጾመው፡፡ ምንም እንኳ በዐቢይ ጾም መቀደስን ግብጽ ብትጀምረውም በእኛ ጾመ ድጓ እና ሰዓታት ስለሚቆም በቅዳሴ ማሳረጉን ብዙ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በከበሮ በማኅሌት ማሸብሸብ ጾም ከመሻር ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዚህም ነበር የጥንተ ስቅለቱ የመጋቢት መድኃኔ ዓለም በዓል በጥቅምት መድኃኔዓለም፣ የመጋቢት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓልም በጥቅምት፤ መጋቢት ዐሥር የነበረው መስቀሉ የተገኘበትም በዐል ከደመራ ሥርዓት ጋር ተገጣጥሞ ቅዳሴ ቤቱም ስለሆነ መስከረም 17 እንዲከበሩ የተወሰነላቸው፡፡ ዛሬም በታላላቅ ቦታዎች ይህ ሥርዓት እንደጸና ይገኛል፡፡
ይህን ሁሉ የምዘረዝረው ግን እንኳን በዐለ ስቅለት ዐቢይ ጾምና ሕማማት እንኳ ምን ያህል የተከበሩ ከባድ በዓላት እንደሆኑ ለመጠቆም ነው፡፡ በሥርዓታችን መሠረት ከሆነ በሕማማት ቤተ ክርስቲያን ለመሔድ ግብረ ሕማማት ለመስማትና ያቅሙን ያህል ለመስገድ ያልቻለ ሰው ቢኖር ከበዓለ ሐምሳ በኋላ ሰኔ ጾም እንደገባ ግብረ ሕማማትም እንዲሰማ ስግደቱንም እንዲሰግድ ታዝዟል፡፡ ስለዚህ እነዚህ በዓላት ምን ያህል ታላቅና ከሌሎቹ ጋር ሊነጻጸሩ እንደማይችሉ በደንብ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ከመሠረቱ የበዓሉ ምንነት ከገባን የስቅለት ዕለት በተደረበ በዓል ምክንያት ይሰገዳል አይሰገድም የሚለው ክርክር ሊፈጠር አይችልምና፡፡ ስለዚህ በስቅለት ዕለት ቀርቶ በሰሙነ ሕማማት በየትኛውም ዕለት እንዳይሰገድ የሚከለክል ምንም ዐይነት በዓል የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ቢኖር ኖሮ ቅዳሴም ይቀደስ ነበር፤ ያ ሁሉ ሥርዓትም አይሠራም ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ግን በዕነዚህ ዕለታት ምክንያት ጸብና ክርክር መነሣት ስለሌበት ተለያይቶና ተጣልቶ በልብም እየተናናቁና እየተነቃቀፉ ከማክበር ተስማምቶና ተከባብሮ አንዱን ማድረጉ የተሻለ መሆኑን በማሰብ ራስን ከክርክርና ከጸብ መቆጠቡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ በዓሉም የሚሻው ዐቢይ ነገር ነው፡፡ በእልህ ከሚቀርብ ማንኛውም አምልኮት በፍቅር የሚፈጸም መታዘዝ ይሻላልና፡፡
በዲ/ን  ብርሃኑ አድማስ