የቅዱስ ሚካኤል ንግስ በትላንትናው ዕለት በታላቅ ድምቀት ተከበረ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!

በትላንትናው ዕለት  በደብራችን በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአምላክ ባለሟል የቅዱስ ሚካኤል በዓል ብፁዕ አቡነ አትናቲዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የድሬደዋና አካባቢዋ  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው የወንጌል አርብኞች መካከል አንዱ መምህር ምሕረተአብ አሰፋ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል። ከትላንት በስቲያ ከዋዜማ ፕሮግራም ጀምሮ ለሊት በማህሌት ከ2AM ጀምሮ በማህሌት፣ በቅዳሴ፣ በወንጌል ትምህርት፣ በኋላም ታቦቱ በብፁዐን አባቶች፣ በደብሩ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን እና ከሩቅም ከቅርብም ከመጡ ምእመናን ጋር በመሆን በዝማሬና በእልልታ  እየታጀበ ዑደት ካደረገ በኋላ በታላቁ አባት በአቡነ አትናቴዎስ ቃለ ምእዳንና ቡርኬ ተሰጥቶ ታቦቱ ወደመንበሩ ባማረ እና በደመቀ ሁኔታ ተመልሷል። ይህን በዓል ለየት የሚያደርገው የህዳር ሚካኤል ታቦተ ንግስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአውደ ምህረቱ ላይ ሆኖ ነበር የሚባርከው ነገር ግን ትላንት በእግዚአብሔር ቸርነት አየሩ ጥሩ ስለነበር ታቦቱ  ወጥቶ ዑደት ተደርጓል። እግዚአብሔር አምላክ የከበረበት ጠላት ዲያቢሎስ ያፈረበት ሆኖ ተጠናቋል ክብር ለድንግል ማርያም ልጅ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !