5ኛው ሳምንት፦ ደብረ ዘይት

ይህ ዕለት ደብረ ዘይት ይባላል። ስያሜው እንደቀደሙት ሰንበታት ሁሉ የቅዱስ ያሬድ ስያሜ ሲሆን በዚህ ቀን መድኃኒታችን ሁለተኛ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በመለኮታዊ ግርማው በሰው መጠን) እንደሚመጣ የዓለምም ፍጻሜው እንዴት እንደሚሆን ለሐዋርያት በደብረ ዘይት ማስተማሩን እንዲሁም በክብር ያረገው ጌታን ለሚጠባበቁት ዋጋቸውን ላልተቀበሉትም ፍዳቸውን ሊከፍል የምድርን ሥርዓት ሊሽር ሰማይና ምድርን አሳልፎ ለወዳጆቹ መንግስቱን ሊያወርስ የቅዱሳንንም እንባ ከዓይናቸው ሊያብስ ኃጥአንን ሊወቅስ ጻድቃንን ሊያወድስ (ብሩካን ብሎ) መምጣቱን እያሰበች ቤተ ክርስቲያን ፈጣሪዋን ታመልካለች። ቅዱስ ያሬድም ይህንኑ ትምህርት በመዝሙሩ ጠቅሶ ስለዘመረውና በዚህ ቀንም እንዲዘመር ስለተደረገ ዕለቱ በባለዜማው ይትበሃል ደብረ ዘይት ይባላል።