የጥምቀት በዓል በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በደመቀ መልኩ ተከበረ

Video 1 

Video 2

ጥር 11 ቀን 2007 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።

Timket5የ2007 ዓ.ም የጥምቀት በአል በሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቁጥሩ በመቶዎች የሚገመት ምእመን በተገኘበት እጅግ ደማቅ በሆነ ኃይማኖታዊ ሥነ ሥርአት ተከበሮ ዋለ።

በደብራችን የሚገኙት አራቱም ታቦታት ማለትም የቅዱስ መድኃኔዓለም፣ የቅድስት ኪዳነምሕረት፣ የቅዱስ ሚካኤልና የቅዱስ ገብርኤል ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እውደት በማድረግ ኅዝቡን የባረኩ ሲሆን ምእመናኑም በከፍተኛ እልልታና ጭብጨባ በመታገዝ የተለያዩ መንፈሳዊ መዝሙራትን በመዘመር ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ውለዋል።

በተለይም በአሉን ለማድመቅና ምእመናኑን በዝማሬ ለማገልገል በእለቱ በእንግድነት የተገኘችው ዘማሪት ፀዳለ ጎበዜ ልዩ በሆነ ጣእመ ዜማ ያላቸውን መዝሙራት በመዘመርና ምእመናንም አምላካቸውን በዝማሬ እንዲያመሰግኑ በማድረግ ለበአሉ ልዩ ድምቀት ሰጥታው ውላለች። በተጨማሪም ሰባኬ ወንጌል ዲያቆን ቸርነት ይግረም ከርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ዋሽንግተን ዲሲ በእንግድነት በመጋበዝ ስለበአሉ ታሪክ ሰፋ ያለና ጥልቅ የሆነ ትምህርት ሰጥተዋል። በአሉ ከተከበረበት እለት ዋዜማም በርካታ ምእመናን የተገኙበት የዋዜማ ታላቅ ጉባኤ የተደረገ ሲሆን በዚህም እለት ዘማሪት ፀዳለ ጎብዜ እና መምህር ቸርነት ይግረም የዝማሬ እና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሰጥተዋል።

የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ባለፋት በርካታ ወራት የደረሰበትን ፈተና ሁሉ በመድኃኔዓለም እርዳታ በመወጣት በስፋት ሲያበረክት የኖረውን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ወደላቀ ደረጃ ከፍ በማድረግ እጅግ ማራኪና ውብ በሆነ ሁኔታ የጥምቀትን በአል በማክበሩ በርካታ ምእመናንን እንባ እየተናነቃቸው ፈጣሪያቸው ላደረገላቸው ተሰፍሮ ለማያልቅ ውለታው ከፍ ያለ ምስጋና ሲያሰሙ ተስተውለዋል። በዚህ አጋጣሚ ረጅም ጉዞ በማድረግ በአሉን በልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት በማድመቅ ያገለገሉንን ዘማሪት ፀዳለ ጎበዜን እና ዲያቆን ቸርነት ይግረምን በመድኃኔዓለም ስም ምስጋና ይድረሳችሁ እንላለን።

በጨማሪም በአሉ እጅግ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ያደረጋችሁትን ምእመናንን ባጠቃላይም የቤተክርስቲያናችን ሰበካ አስተዳደር /ቦርድ/ ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር