ጥምቀት ምንድን ነው? ለምንስ እንጠመቃለን?

TimketHannaጥምቀት “አጥመቀ” ከሚለው የግእዝ ቃል/ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም በውኃ ውስጥ መዘፈቅ ወይንም መነከር ማለት ነው። ጥምቀት ከጌታችን እና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በፊትም የነበረ ሰዎች ከህመማቸው ፈውስ የሚያገኙበት ማለትም የሥጋ ድህነት ከሚገኝበት የፈውስ መንገዶች አንዱ ነበረ።

ንእማን የተባለው የእስራኤል ንጉሥ በለምጽ ተመቶ ሳለ ወደ ነብዩ ኤልሳዕ ዘንድ በመሔድ ነብዩ እንደነገረው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ተፈውሷል።2ኛ ነገ. ም. 5 ቁ 8-14። በሐዲስ ኪዳንም ተጽፎ እንደምናገኘው 38 ዓመት በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የነበረው ሰው እንደመሰከረው በሰሊሆም ቤተሳይዳ ውኃ ሰዎች እየተጠመቁ ፈውስ ያገኙ እንደነበረ እርሱ ግን ወደ ውኃው የሚወስደው በማጣቱ በዚያ እንዳለ ለጌታ መንገሩ ሌላው ማስረጃ ነው። ዮሐ.ወን. ም.5 ቁ.2-9። ጌታን ያጠመቀው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም ሥራው ንሰሀን መስበክ፣ ሰዎችን በውኃ ማጥመቅ እና ከሥጋ በሽታ መፈወስ ነበረ።” እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።” የማርቆስ ወንጌል 1:2-5። ስለሆነም በውኃ ተጠምቆ ፈውስ ማግኘት አስቀድሞም የነበረ ነው።

የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ግን ከእነኝህ ሁሉ ጥምቀቶች የተለየ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት አስቀድሞ ታሪካቸው ከውኃ ጋር በተገናኘ የተፈጸሙ የታሪክ ክንውኖችን አካቶ ምሳሌነታቸውን የገለጠ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአዳምና በሔዋን ምክንያት በሰው ልጆች ላይ ደርሶ የነበረውን ፍርድ የቀየረና የደመሰሰ የዘለዓለማዊ ሕይወት ፈር ቀዳጅ እና የእግዚአብሔር ልጅነት ማረጋገጫ የሆነ የድኅነት መሠረት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባቸው መሠረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ናቸው?

  1. የዕዳ ደብዳቢያችንን ለመደምሰስ ተጠመቀ
    ዲያቢሎስ አዳም እና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዲያፈርሱ ካደረገ በኋላ እስከመጨረሻው የእርሱ ባርያና አገልጋዮች ይሆኑለት ዘንድ በሁለት ድጋዮች ላይ አዳም ግብሩ ለዲያብሎስ ሄአዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብሎ አጻፋቸው። ያንን ጽሑፍም ወስዶ አንደኛውን በዮርዳኖስ ወንዝ አንደኛውን ደግሞ በሲዖል አስቀምጦ ነበር። ጌታ ወደዚህ አለም የመጣው አዳምን እና ሔዋንን ከባርነት ነጻ ለማውጣትና ድኅነት ሊሆናቸው ነውና በጥምቀቱ ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ በሰይጣን ተቀብሮ የነበረውን የእዳ ደብዳቤያቸውን ረግጦ እና አቅልጦ አጠፋላቸው። በሲዖል የተደበቀውን ደግሞ በእለተ ስቅለት አርብ ሲኦልን በበዘበዘ ጊዜ አጥፍቶታል። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሮታል። “ እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።” ቆላ.2፡13-14
  2. ትሕትናንን ለማስተማር ተጠመቀ
    ይህም እግዚአብሔር አምላክ የትሕትና መምህር መሆኑን ለማሳየት በፈጠረው በሰው እጅ ራሱን ዝቅ አድርጎ ተጠምቋል። በምሴተ ሐሙስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሰዎችን እግር እንዳጠበ እና ትህትናንን እንዳስተማረ ሁሉ አስቀድሞም በጥምቀቱ ትህትናን አስተምሯል። “ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው።” ማቴ. 3፡ 15
  3. ምሥጢረ ሥላሴን ለመግለጥ ጌታ ተጠመቀ
    እግዚአብሔር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ እና ይህን በመሳሰሉት ሁሉ አንድ አምላክ ነው። ነገር ግን በስም፣በአካል፣ በግብር ሦስት ነው። ይህም ታላቅ ምስጢር በይፋ የተገለጸው በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው። “ያን ጊዜ ፈቀደለት።ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።” ማቴ.3፡ 16-17
  4. አርአያ ሊሆንን ተጠመቀ
    ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ መጠመቅ ግዴታው ነው። ይህም ደግሞ ማድረግ እንደሚገባ ለሰዎች አርአያ በመሆን እርሱ ራሱ ተጠምቆ ምሳሌነትን ትቶልናል። ስለዚህም ጥምቀቱ ለሰዎች አርአያነትም የተደረገ ነው።
    ጌታችን ከመጠመቁ በፊት ብዙ ተዓምራትን አድርጓል። እንደሰውም በመጠን በማደግ ሕግን ሁሉ ከኃጢያት በቀር ፈጽሟል። ነገር ግን ጌታ ዋናውን የማዳኑን ሥራ በይፋ የጀመረው በጥምቀት ነው። በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ በቀጥታ ወደ ገዳም ሄዶ 40 ቀን እና ሌሊት ጾመ። ከገዳምም ወጥቶ ወደ ሠርግ ቤት ወደ ቃና ዘገሊላ ሄዶ የመጀመሪያውን ተአምር በይፋ አደረገ። ዮሐ. ወን. ም.2 ቁ. 11 ። ከዚያም እስከ እለተ ስቅለቱ ድረስ እያስተማረና እየፈወሰ ተዓምራትን እያደረገ ኖረ። በመጨረሻም ጥምቀቱ እንደ ምሳሌ የሆነውን የመጨረሻውን የማዳኑን ሥራ በመስቀል ሞቶ መነሳትን አከናወነ። የጌታ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሙትና መቃብርን ድል ነስቶ መነሳቱ አስቀድሞ በጥምቀቱም የተመሰለ ነበረ። ዛሬም ክርስቲያኖች በ40 እና በ80 ቀን የልጅነት ጥምቀት ስንጠመቅ ይህንኑ ምስጢር በማመልከት ምስጢረ ጥምቀቱን እና ምስጢረ ትንሳዔውን በሚያጠይቅ መልኩ እንጠመቃለን። በ40 እና በ80 ቀን መጠመቃችን አዳም እና ሔዋን የልጅነት ጸጋ ያገኙ በ40 እና በ80 ቀን በመሆኑ ሲሆን በመጽሐፍም ወንድ በተወለደ በ40 ቀን ሴት በተወለደች ደግሞ በ80 ቀን የመንጻት ሥርአት እንዲደረግ የታዘዘ በምሆኑም ጭምር ነው። ዘሌ. 12፡ 1-9። ሦስት ጊዜ በውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ አድርጎ ካህኑ ሕፃኑን/ሕፃኗን ሲያጠምቅ ጥምቀቱን በሚመስል ጥምቅት ከክርስቶስ ጋር እነተባበራለን፡፤ ከሰማይ ወርዶ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን እንደተነሳም መጀመሪያ ወደ ውኃው ስንነከር ከሰማይ መውረዱን ከዚያም በከርሰ መቃብር ማደሩን ሙትና መቃብርን አጥፍቶ መነሳቱን በሚያመለክት ከውኃው በመውጣት ይህንም 3ጊዜ በመፈጸም ምስጢረ ጥምቀትን ከሚስጥረ ትንሳኤ ጋር በማስተባበር ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ልጅነትን በመስጠት እና በማስማር ትመሰክራለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው “ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት
    ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። እንዳለ ቆላ. 2፡ 12-12

ጥምቀት ያስፈለገበትን ዋና ዋና ነጥቦች/ምክንያቶችን እንደሚከተለው እንመለከታለን

  1. ጥምቀት የእግዚአብሔርን ልጅነትና ድኅነትን የምናገኝባት ናት
    በማርቆስ ወንጌል 16:16 ላይ ጌታ ራሱ እንደነገረን ድኅነት የሚገኘው አምኖ በመጠመቅ ስለሆነ ለሰዎች ከሁሉ በፊት መከናወን ያለበት ጥምቀት ነው። ማንም ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ሊባልና ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ የሚችለው በጥምቀት ብቻ እንደሆነም አምላካችን አስረግጦ አስተምሮናል። ይህም ትምህርት ጌታ የፈሪሳውያን ምሁር ከነበረው ከኒቆዲሞስ ጋር ባደረገው ጥያቄና መልስ በዮሐንስ ወንጌል ም. 3 ከቁጥር 1 እስከ 7 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። “ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።”
  2. ጥምቀት ሥርየተ ኃጢያትን ታሰጣለች
    በሐዋርያት ሥራ ም. 22 ቁ. 16 ላይ እንደተመዘገበው አስቀድሞ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታ በደማስቆ መንገድ ላይ ከመታው በኋላ አይነ ስውር ሆኖ ሳለ ሐናንያ ወደተባለው ሰው ዘንድ ሄደ። በዚያም ከሐጢያቱ እንዲነጻ ቅዱስ ጳውሎስን ተነሳና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢያትህም ታጠብ አለው። እንዲሁም አደረገ ፈውስንም አገኘ። በዚያው በሐዋርያት ሥራ ላይ ም.2 ቁ. 37 ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተማራቸው ሰዎች አሁንስ ምን እናድርግ? ቢሉት ንስሐ ግቡ ኃጢያታችሁ ይሰረይላችሁ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ብሎ ነበር ያዘዛቸው። በምዕራፍ 8 ቁ. 38 ላይም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንዳልጠመቅ ምን ይከለክለኛል ብሎ ሐዋርያው ፊሊጶስን በጠየቀው ጊዜ ምንም የሚከለክለው እንደሌለ ነግሮት በውኃ ተጠምቆ ኃጢያቱን ማስተሰረይ ብቻ ሳይሆን ክርስትናንም ወደኢትዮጵያ አምጥቶልናል። በዚህም አይነት በጥምቀት ኃጢያታችንን አስተሰርየን አዲስ ሕይወት እናገኛለን ማለት ነው።
  3. በጥምቀት የክርስቶስ እና የቤተክርስቲያን አካል በመሆን ክርስቶስን እንመስለዋለን
    ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው በዋናነት ለድኅነትና ለአርአያነት ነው። እርሱ ያደረጋቸውን ነገሮች በማድረግ ወይንም አርአያ ሆኖ እንድናደርጋቸው ያሳየንን ነገሮች በማድረግ ክርስቶስን በሥራ እንመስለዋለን። ከነዚህም ውስጥ አንዱ ጥምቀት ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ጌታን በሞቱ የምንመስለው በጥምቀት ነው። በገላትያ መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን እንዲህ በማለት ያስረዳል፦
    “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡” ገላ. 3:27 በቀደመው ዘመን ሰዎች የአብርሃም ወገን የእግዚአብሔር ሰዎች ምሆናቸው ምልክት የነበረው ግዝረት ነበረ። በአዲስ ኪዳን ግን ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው የሚታወቅበት ምልክት ጥምቀት ነው። ስለሆነም አንድ ሰው የቤተክርስቲያን አካል፣አባል መሆኑ የሚታወቀው በጥምቀት ነው።

የጥምቀት አይነቶች

  1. የውሃ ጥምቀት፦ በስፋት የነበረና ያለ ነው። ከላይ እንዳየነው ጌታም የተጠመቀው አርአያም የሆነን በውኃ ተጠምቆ ነው። የውሃ ጥምቀት ሁሉን እኩል የሚያደርግ ደሃ ሃብታም ሳይባል የሚሰጥ ጥምቀት በመሆኑ ጌታም በውሃ መጠመቁ አብይ ምክንያቱ ይህ ነው።
  2. በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ፦ እግዚአብሔር ለፈቀደላቸውና ለተመረጡ ነው። ሐዋርያት በእለተ ጰራቅሊጦስ በዝግ ቤት ሳሉ በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቁ።ሐዋ.ሥ.2:3
  3. የደም ጥምቀት፦ይህኛው ጥምቀት ካለማመን ወደማመን የተመለሱ ሰዎች ለሚስጥረ ጥምቀት ሳይደርሱ ለምን ወደ ክርስትና ገባችሁ ብለው አሕዛብና ክፉዎች ቢገድሏቸው የፈሰሰው ደማቸው እንደ ጥምቀት ይቆጠርላቸዋል። ወይንም ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው ሲሉ ደማቸውን እስከማፍሰስ ራሳቸውን አሳልፈው ሲሰጡ በማየት ያላመኑ ሰዎች በዚህ የእምነት ጽናት ተነሳስተው እነዚህ ክርስቲያኖች በሚያምኑት አምልክ አምናለሁ በማለት እነርሱም ሰማእትነትን ቢቀበሉ ደማቸው ጥምቀት ይሆንላቸዋል ማለት ነው።
    ሚስጥረ ጥምቀት የሚፈጸመው በማን ነው?
    ሚስጥረ ጥምቀት የሚፈጸመው የክህነት ሥልጣን ባለው ሰው ብቻ ነው። ይህም በማቴዎስ ወንጌል 28፡19-20 ላይ ሒዱና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ብሎ ሐዋርያትን በማዘዙ እንዲሁም በማቴዎስ 18 ላይ እናንተ ያሰራችሁት የታሰረ ነው የፈታችሁም የተፈታ ነው ብሉ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ቃል መሠረት በማድረግ ነው።

የጥምቀቱ በረከት በሁላችንም ላይ ይደር።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።