በአብይ ጾም ውስጥ ያሉ ሳምንታት ስያሜ

የተከበራችሁ የቤተክርስትያናችን አባላት እና ቤተሰቦች በሙሉ፤
እንኳን ለ2016 ዐብይ ጾም አደረሰን!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለጾም ሥርዓት እና ደንብ አውጥታ በዓመት ውስጥ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት እንዳሉና ማንኛውም ክርስቲያን እነኝህን አጽዋማት እንዲጾሙ ታዛለች። ከነዚህም አንዱ እና ታላቁ ጾም ዛሬ ሰኞ መጋቢት 2/2016 (March 11, 2024) የጀመርነው የአብይ ጾም ነው:: ለዚህም ቤተክርስቲያናችን እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቷን ትገልጻለች።

ዐቢይ ጾም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ የጾመው ጾም እና ለእኛ አራያ የሆነበት ጾም ነው። እኛም እንድንጾማቸው በቤተ ክርስቲያናችን ከታዘዝናቸው ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ ነው። እኛ ምእመናን ጌታችን ያደረገውን ምሳሌ ተከትለን ጾሙን በየዓመቱ እንጾመዋለን። ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት (፶፭ ቀኖች) ሲኖሩት በውስጡ ስምንት ቅዳሜዎች፣ ሰባት እሑዶች ይገኛሉ።እነዚህም ዐሥራ አምስት ቀናት ሲሆኑ በእነዚህ ቀናት ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጦሙ እነዚህ ቀናት ሲቀነሱ የጦሙ ወራት ዐርባ ቀን ብቻ ይሆናል።

ዓብይ ጾም የተባለበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ስለሆነና ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎችን ድል የተነሱበት በመሆኑ ዛሬም ክርስቲያኖች የአምላካችንን አርአያ ተከትለን ሰይጣንን ድል የምንነሳበት ጾም ስለሆነ ነው።

የዐብይ ጾም በተለያዩ ስሞችም ይጠራል

  • ሁዳዴ ጾም ይባላል። ይህም የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥፍራ ሁዳድ ይባላል። በመሆኑም ዐቢይ ጾምም ከአጽዋማት ሁሉ ብዙ ቀናት ስለሚጾምና ክርስቲያኖች የሆኑ ምዕመናን ሁሉ ስለሚጾሙት የሁዳዴ ጾም ተባለ።
  • ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ፵ ቀን ስለሆነ ጾመ ዐርባ ም ይባላል /ማቴ.፬፥፩/

በአብይ ጾም ውስጥ ያሉ ሳምንታት ስያሜ

  • ዘወረደ
  • ቅድስት
  • ምኵራብ
  • መጻጕዕ
  • ደብረዘይት
  • ገብርኄር
  • ኒቆዲሞስ
  • ሆሳዕና
  • ትንሳኤ ናቸው ::

የደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በአብይ ጾም ያላት የአገልግሎት መርኃ ግብር

  • ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ ከጠዋቱ 6 ኤ.ኤም እስከ 10 ኤ.ኤም የኪዳን ፀሎት አገልግሎት ይሰጣል።
  • ዘወትር ቅዳሜ ከጠዋቱ 6 ኤ.ኤም እስከ 8 ኤ.ኤም የኪዳን ፀሎት ይደርሳል።
  • ዘወትር እሁድ ከንጋቱ 3 ኤ.ኤም ጀምሮ የፀሎት፣ የክርስትና፣ የቅዳሴ አገልግሎቶች ይሰጣል::

ከዘመድ እና ከወዳጅ ጋር በመምጣት የበረከቱ ተካፊይ እንዲሆኑ የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።

በሚኒሶታ የደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የአገልግሎት ቀን መቁጠሪያ ::

  • የዓብይ ጾም (የሁዳዴ ጾም) :- ከመጋቢት 2 አስከ ሚያዝያ 27 (Monday March 11, 2024 – Sunday May 5, 2024)
  • መጋቢት መድሐኔዓለም :- በዓለ ንግሱ መርኃ ግብር የሚከናወንበት ትክክለኛ ቀን : መጋቢት 29, 2016 (Sunday Apr. 7, 2024) / Megabit Medhanealem / The original Crucifixion.
  • ደብረ ዘይት :- መጋቢት 29, 2016 (Sunday April 7, 2024) / Debrezeit
  • ሀሳዕና :- ሚያዝያ 20, 2016 (Sunday April 28, 2024) / Hosanna
  • ሰሙነ ሕማማት :- ሚያዝያ 21, 2016 እስከ ሚያዝያ 26, 2016 (Monday April 29, 2024 to Friday May 3, 2024) / Holy/Passion week.
  • ጸሎተ ሐሙስ :- ሚያዝያ 25, 2016 (Thursday May 2, 2024) / Maundy Thursday
  • ስቅለት :- ሚያዝያ 26, 2016 (Friday May 3, 2024) / Good Friday (Crucifixion)
  • ትንሣኤ :- ሚያዝያ 27, 2016 (Sunday May 5, 2024) / Easter Sunday

በዚህ አብይ ጾም ሁላችም ስለሀገራችን እና ስለ ቅድስት ቤተክርስትያናችን አብዝተን የምንጸልይበት እኛም በረከት የምናገኝበት በስጋ ወደሙ የምንከብርበት ያድርግልን::

ጽሁፉን ያዘጋጀችው ወይዘሮ ሐና ስዩም ነች::

አድራሻችን: 4401 Minnehaha Avenue S., Minneapolis, MN 55406
ስልክ: (612) 721-1222
ኢሜይል: dsmachurch@gmail.com
ዌብሳይት: https://www.debreselam.net
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/Debreselameotc/