እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!

በሥመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱሥ አሀዱ አምላክ አሜን!!!

በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። መዝ ፷፬፥፲፩

የተከበራችሁ የቤተክርስትያችንና አባላት እና ቤተሰቦች በሙሉ፤
እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ እያልን መጭው ዓመት የሰላም ፣ የጤና እንዲሁም የፍቅር ዓመት እንዲሆንላችሁ በሚኒሶታ የደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የአስተዳደር ቦርድ እየተመኘን እንደወትሮዉ ሁሉ በዚህ ባጠናቀቅነዉ የ፪ሺ፲፭ ዓ.ም የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዓመቱን በሙሉ ክፍት ሆና ዘወትር በየአዘቦት ቀናቶች የኪዳን አገልግሎት፣ ዘወትር እሁድ የኪዳን ፀሎት፣ ቅዳሴ እና ማህሌት፣ እንዲሁም የንግሥ በአላት ፀሎት እና የቅዳሴ አገልግሎቶች፣ የክርስትና፣ ቅዱስ ጋብቻ፣ ፀሎተ ፍታት አገልግሎቶችን ሰጥታለች::

እንደሚታወቀው ሁሉ ደብራችን የሚንቀሳቀስው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በበጎፈቃደኞች ግልጋሎት እና እገዛ ነው:: እንደወትሮው ሁሉ በዚህ አመትም ብዙ የደብራችን አባላት በተለያዩ የስራ ዘርፎች በፈቃደኝነት በመሳተፍ ውድ ጊዜአቸውን ጉልበታቸውን እውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን በተለያዮ ጊዜእት ለቤተክርስቲያናችን አበርክተዋል:: ለመጥቀስም ያህል በቤተክርስታያን ጽዳት ምግብ ሻይና ቡና በማቅረብና በማዘጋጀት በአባላት ማህበራት ውስጥ በአመራርነት በመሳተፍ ህጻናትን እና ወጣቶችን በመንፈሳዊ እውቀት እና በግብረገብነት በማነጽና በመምራት ህንጻ ኮሚቴ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ላይ በበጎፈቃድ የስራ ቦታዎች በመሳተፍ በመንፈሳዊ አገልግሎቱም በኩል በበጎፈቃደኝነት በመሳተፍና በሌሎችም እዚህ ባልተጠቀሱ ግልጋሎቶች ሁሉ በመሳተፍ:: በዚህ አጋጣሚ የአስተዳደር ቦርዱ ለደብራችን በጎፈቃደኞች ሁሉ የከበረ ምስጋናውን ያቀርባል:: መድሀኔአለም በበረከቱ ይጎብኛችሁ::

በተጨማሪም በ፪ሺ፲፭ ዓ.ም. ዘርፈ ብዙ የሆኑ ልዩ ልዩ ማህበራዊ እና ትምህርታዊ አገልግሎቶች ተሰጥተዋል:: ለመጥቀሰም ያህል:-
1. ወጣቶች ስርዓተ ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ በሊቃውንት አባቶች የድቁና ትምህርት ተሰጧቸው ድቁንና ተቀብለዋል::
2. በበጎፈቃደኞች
እርዳታ ለልጆችና ወጣቶች መንፈሳዊ የበገና ትምህርት ተሰጧቸዋል።
3. በበጎፈቃደኞች እና በወላጆች እርዳታ ልጆችና ወጣቶች መንፈሳዊ እና የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን ይከታተሉባታል::

የ፪ሺ፲፭ ዓ.ም. ልዩ ልዩ ተጨማሪ ክንዋኔወችን በሚመለከት:-
4.
ደብራችን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የአስተዳደር ቦርድ አባላት ምርጫ ለ12ኛ ጊዜ ተካሂዶ አዲስ የተመረጡት የአስተዳደር ቦርድ አባላት የሶሰት አመት የስራ ዘመናቸውን ቃለ መሀላ በመፈፀም ጀምረዋል::
5. በዚህ በጨረስነው አመት 68 ቤተስቦች ደብራችንን በአዲስ አባልነት ተቀላቅለዋል:: እንኳን ደህና መጣችሁ እንላቸዋለን::
6. ቤተክርስቲያናችን
12 ክፍል እና ከኮሌጅ ትምህርታቸዉን ላጠናቀቁ 12 የቤተክርስቲያናችን ወጣቶች የእንኳን ደስ ያላችሁ የምስክር ወረቀት አበርክታለች::
7. አዲሱን የቤተክርስቲያናችንን ሕንፃ ለመገንባት የሚያስፈልገንን ገንዘብ ለማሰባሰብ ከኪሳችን ከምናዋጣው ገንዘብ በተጨማሪ ነፃ የበጎፈቃደኝነት የገንዘብ ማሰባስቡን ስራ እንደወትሮዉ ሁሉ በዩኤስ ባንክ ስታዲየም ቀጥለንበት እንገኛለን:: በዚሁ በተጠናቀቀው የ፪ሺ፲፭ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚኒሶታ ስቴት ፌር የስራ መስክ ተቀይሶ በበጎፈቃደኝነት
አገልግሎት የገንዘብ ማሰባስቡ ስራ በጥሩ ውጤት ተጠናቋል::

8. አባላት እና ቤተሰቦቻቸው በፌለን መናፈሻ ውስጥ ለዘጠነኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የ5,000 ሜትር ሩጫና እርምጃ መርኃ ግብር በደመቀ መልኩ ተሳትፈው መርኃ ግብሩ በሰላም ተጠናቋል:: በእለቱም አሸናፊዎች የተዘጋጀላቸውን ሜዳልያና ምስክር ወረቀት ከደብራችን አስተዳዳሪ ከመልአከ ጽዮን ቀሲስ አዲስ ሞላው እና ከመርኃ ግብሩ አዘጋጆች ተቀብለዋል::

9. በዚሁ በተጠናቀቀው በ፪ሺ፲፭ ዓ.ም. የቤዛ ኩሉ ሰንበት ትምህርት ቤት የ27ኛ ዓመት ምስረታ በዓል በሚኒሶታ የደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ውስጥ በድምቀት ተከብሯል።

10. በዚሁ በተጠናቀቀው በ፪ሺ፲፭ ዓ.ም. ለህጻናት ታዳጊዎችና ወጣቶች ለአንድ ሳምንት የቆዬ የሰመር ካምፕ ዝግጅቶች በጥሩ ውጤት እና በሰላም ተጠናቋል:: የሰመር ካምፑ የተለያዩ ልጆችን የሚስተምሩ እና የሚያዝናኑ ዝግጅቶች ነበሩት::

11. በዚሁ በተጠናቀቀው በ፪ሺ፲፭ ዓ.ም. ለሁለት ሳምንት የቆዬ የልጆች ሰመር ኮርስ (summer courses) በሰላም ተጠናቋል::

12. በዚሁ በተጠናቀቀው በ፪ሺ፲፭ ዓ.ም. ከዶ/ር ሲራክ በተገኘ የበጎፈቃደኝነት የገንዘብ እርዳታ ህጻናት ታዳጊዎችና ወጣቶችን ያሳተፈ በበንከር የውሀ ዳርቻ (Bunker beach) እና Valley Fair የመዝናኛ እና የሽርሽር ጉዞ (field Trip) በደመቀ መልኩ ተጠናቋል::

አዲሱ ዘመንም የሰላም እና የጤና እንዲሆንላችሁ ከልብ እንመኛለን:: በ፪ሺ፲፮ዓ.ም ቃለ እግዚአብሔር ለመማር፣ ንስሐ ለመግባት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ያብቃን።

ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ብለን የምናመሰግነው፣ ዘመናትን የሚያስረጃቸው፣ ዘመናትን የፈጠረ እና ሰፍሮ ለሰው ልጅ የሰጠ ልዑል እግዚአብሔር መጨው ፪ሺ፲፮ ዓመተ ምህረትን ባርኮ ለቤተክርስቲያን ይስጥልን፤ የመከራውን ዘመንም በቃ ይበለን፤ የእመአምላክ እናትነቷ ምልጃና ርህራሄ አይለየን ፤ አስራት ሀገሯን ኢትዮጵያም በቀደመ ክብሯ ታስብልን አሜን!!!

በሚኒሶታ የደብረሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የአስተዳደር ቦርድ
መስከረም ፩ ፪ሺ፲፮ ዓ.ም
ሚኒአፖልስ ሚኒሶታ
September 12, 2023, Minneapolis, Minnesota, U.S.A.

ለተጨማሪ ማብራሪያ ጥያቄ ካለዎት?
እርስት መኮንን 952-221-6668
ደባልቄ ገበየሁ 612-203-7745

አድራሻችን: 4401 Minnehaha Avenue S., Minneapolis, MN 55406
ስልክ: (612) 721-1222
ኢሜይል: dsmachurch@gmail.com
Website: https://www.debreselam.net
Facebook: https://www.facebook.com/Debreselameotc/