ዐብይ ጾመ

እንኳን እግዚአብሔር አምላክ ለዚህ ታላቅ ጾም በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን!

ይህንን ጾም በእስር ቤት ላሉት ለታመሙት ለተጨነቁት ወገኖቻችን እግዚአብሔር  የቸርነቱን ሥራ ይሰራላቸው ዘንድ በፀሎት ፤በሐሳብ ከእነሱ ጋር እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን ጾሙንም የኀጢአት መደምሰሻ የዲያብሎስ ድል መንሻ የመንግስተ ሰማያት መውረሻ ያድርግልን።

ዐቢይ የሚለው ቃል ዐብየ ከፍ ከፍ አለ ከሚለዉ የግዕዝ ግስ የወጣ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ታላቅ ማለት ነው፤ ይህንን ጾም አባቶቻችን በተለያየ ስያሜ ጠርተውታል፣ ጌታ እራሱ የጾመው ስለሆነ የጌታ ጾም በመባል ይጠራል በጾሙም ወቅት ሦስቱ የሰይጣን ፈተናዎች ማለትም ትዕቢት፣ ስስት፣ ፍቅረ ነዋይ ድል ተመተውበታል ጾሙም ብዙ መንፈሳዊ በረከት ስለምናገኝበት ጾመ ሁዳዴ በመባልም ይጠራል።

ጾሙ በድምሩ 55 ቀን ይጾማል ጌታ የጾመው 40 ቀን አይደል? ለምን 55 ሆነ ቢሉ

የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ተብሎ ይጠራል ንጉስ ሕርቃል 614 ዓ/ም ኪርዮስ የሚባል የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመዉረር ጥቃት አደረሰ ንግሥት ዕሌኒ በሰራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግስቷ አስቀምጣው የነበረውን የጌታን መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አየው ቢነካው አቃጠለው  ከዚያም የቤተ መቅደስ አገልጋዮችን አሸክሞ ንዋየ ቅዱሳቱን ዘርፎ 60ሺህ የሚደረርሱትን አቁስሎ ከ3000ሺህ በላይ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋን አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል በዚህን ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንግሩ የተሸሸጉት ተሰብስበው ለንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል ሕርቃልም ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ድል ተቀዳጀ የተማረኩት ሁሉ ነፃ ወጡ ስለዚህ መስቀል ከምርኮ እንደተመለሰ እኛም ከኀጢአት ምርኮ እንድንመለስ ለእኛም በኀጢአት ላይ ድል መንሳትን ስጠን ብለን እንጾማለን  የሰይጣንን ትግል ማሸነፍ የምንችለው በጾምና በፀሎት ስለሆነ ከ40ው የጌታ ጾም ጋር ተደምሯል። የእኛ ጠላት የጨለማዉ ገዢ የሆነው ዲያብሎስ ነዉና እሱን በጾም እንድናሸንፍ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል።

የመጨረሻዋ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ደግሞ የጥንት ክርስቲያኖች ከ40 ቀን ውጪ ይጾሙት የነበረዉን ሰሙነ ሕማማት ከጌታ ጾም ጋር ደምረን እንድንጾም ሥርዓት /ቀኖና/ አስቀምጠውልናል።  በቤተክርስቲያን ስያሜ መሰረት በዐቢይ ጾም ዉስጥ የሚውሉ ሰንበታት እያንዳንዳቸው መጠሪያ ሲኖራቸው የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ በመባል ይጠረራል።

  1. 1ኛ ሳምንት፦ ዘወረደ – የዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት የወረደ ፣ የታየ ፣ የተገለፀ ማለት ነዉ ይህውም ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን ፈጥሮ የሚኖር አልፋና ኦሜጋ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንፅሕተ ንፁሐን ከድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመለክት ስያሜ ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ይህንን በማስመልከት ሳምንቱን ስለ አምላክ ወደ ምድር መውረድ መወለድ ታስተምራለቸ  ዮሐ3፥13
  2. 2ኛ ሳምንት፦ ቅድስት – የሰንበት ቅድስና
  3. 3ኛ ሳምንት፦ ምኩራብ – ክርስቶስ በመኩራብ ማስተማሩ
  4. 4ኛ ሳምንት፦ መፃጉ – ክርስቶስ በሽተኞችን መፈወሱ
  5. 5ኛ ሳምንት፦ ደብረዘይት – በደብረዘይት ተራራ ስለ ዳግም ምጽዓቱ ማስተማሩ
  6. 6ኛ ሳምንት፦ ገብርሔር – ለደግ አገልጋይ ዋጋ ያለው መሆኑ
  7. 7ኛ ሳምንት፦ ኒቆዲሞስ – ጌታ ከኒቆዲሞስ ጋር መነጋገሩ
  8. 8ኛ ሳምንት፦ ሆሳዕና – እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱና ስለ እኛ ህማማትን መቀበሉ ይታሰብበታል።

ይቆየን

የደብረ ሰላም ስብከተ ወንጌል ክፍል

ሚኒሶታ