ጥምቀት አይከለስም – የአቡነ አትናቴዎስ እና የአቡነ ዳንኤል መልዕክት

ዜና ደብረሰላም መድኃኔዓለም ዘሚኒሶታ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።
የሜኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም የ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ቤተክርቲያን ዓመታዊውን የጥቅምት መድኃኔዓለም ክብረ በአል ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎና በአማራ ክልል የኦሮሞ ሕብረተሰብ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹእ አቡነ ዳንኤል የድሬዳዋና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ታዋቂው ሰባኪ ወንጌል መምህር ምሕረተአብ አሰፋ በተገኙበት በትላንትናው እለት እጅግ በደመቀና ባመረ ሥነ ስርዓት ተከብሮ ውሏል።
በዚህ ቁጥሩ ከምንግዜውም በላይ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ በተገኘበት በአለ ንግሥ ላይ ከዋዜማው ጀምሮ ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ብጹአን አባቶችም ለታዳሚው ሕዝብ ትምህርት፣ ቡራኬና ቃለ ምእዳን ሰጥተዋል።
ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎና በአማራ ክልል የኦሮሞ ሕብረተሰብ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት አባታዊ ቃለ ምእዳን እና ቡራኬ የሜኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አንዳንዶች እንደሚናገሩት ከእናት ቤተክርስቲያን የተለ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ይህ ባይሆን ኖሮ እኛም የምንወዳቸውን እና የምናከብራቸውን ምእመናን መጥተን ባልባረክናችሁ ነበር ብለዋል። ብጹእነታቸው እንዳሉት እንደ አባቶቻችን ሕግና ሥርአት እምነት አንድ ነው ጥምቀትም አንድ ነው ምናልባት በእምነት የመሰነካከል ነገር እንኳን ቢኖር ለዚያም የተሰራ ሥርዐት አለ ከዛ ውጪ ግን አንድ ግዜ የተሰጠን ጥምቀት መከለስ አይቻልም፤ በጥምቀት ላይ ጥምቀት ቢፈጸም ግን እንደሻወር ነው የሚቆጠረው በማለት በብጹእ አቡነ ዘካርያስ እየተፈጸመ ያለውን ከሕገ ቤተክርስቲያን የወጣ ድርጊት የተሳሳተ መሆኑን አመልክተዋል።
ብጹእ አቡነ ዳንኤል የድሬዳዋና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው የእለቱን በአል የተመለከተ ትምህርት ከሰጡ በኃላ በተለይም ጥምቀትን አስመልክቶ በሰጡት ትምህርት ይልቁንም ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያናት በጥንቃቄ የሚፈጸሙ እንደሆኑ አስረድተው ሚስጢረ ጥምቀትና ምስጢረ ክህነት ፈጽሞ የማይደገሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። ብጹእነታቸው እንዳሉት ጥምቀትን የሚደግም ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እና አባቶች ፍጹም ርምጃ ይወስዳሉ ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህ ክርስትና እንደገና የማንሳትን ተግባር እውነተኛ ኦርቶዶክስ የሆነና ህሊና ያለው ሰው በፍጹም የሚያደርገው ነገር አይደለም ካሉ በኋላ በሌላ ነገር መቀየም ይቻል ይሆናል ይህን ማድረግ ግን ከባድ ቅጣት የሥልጣነ ክህነት መያዝና ውግዘት እንደሚያስከትል አብራርተዋል።
ስለ ሜኒሶታ ደብረሰላም ቤተክርስቲያንም ሲመሰክሩ ይህች ቤተክርስቲያን በብዙ አንጋፋ ብጹአን አባቶች የተባረከች ስለሆነች ምንም አይነት ቅሬታ እና መጠራጠር እንዳይሰማችሁ እናረጋግጥላችኋለን ከዚህች ቤተክርስትያን ወዴትም እንዳትሔዱ እናሳስባችኋለን በማለት ምእመናንን የሚያጽናና እና የሚያንጽ ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ወደዚህ ስንመጣ ምንም አይመስለንም ደስ እያለን ነው የምንመጣው፤ ከዚህ ከወጡት ልጆቻችን ጋርም ሰላምንም ለማምጣት ብዙ ጥረናል አሁንም እየጣርን ነው ብለዋል። ብጹእ አባታችንም /ብጹእ አቡነ አትናቴዎስ/ ብዙ ጥረዋል፤ ሰላም ለማምጣት ስልክ ደውለው ጆሯቸው ላይ ነው የዘጉባቸው ይህን ግፍ እግዚአብሔር እንዳይቆጥርባቸው እንጸልይላቸዋለን ብለዋል።
ቀደም ሲልም መምህር ምሕረታብ አሰፋ ሰፊ የሆነ የወንጌል ትምህርት የሰጡ ሲሆን በማስከተልም ቤተክርስቲያኑ ላለበት የተለያዩ ወጪዎች እና ወደፊት ለመስራት ላቀደው አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ በእለቱ በተደረገ የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት 90ሺህ /ዘጠና ሺህ/ ዶላር ያህል ከምእመናን በጥሬ ገንዘብ በቼክና በቃል መግቢያ ቅጽ ተሰብስቧል።

ስላደረገልን ሁሉ እግዚአብሔር ይመስገን።