ደብረ ሰላም 2.7 Acres (1.1 ሔክታር ወይንም 10927 ካሬ ሜትር) ቦታ ገዛች

2016-06-20 08_32_31-New notification በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።

“የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን” ነህምያ 2፥20

ከሁሉ አስቀድሞ ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ለሰራ ለልዑል እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁን።

ቤተክርስቲያናችን ሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚሰጡባት ንጽሕት እና ቅድስት የሆነች የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት። ይህች ቤተክርስቲያን በፈቃደ እግዚአብሔር ከተመሰረተች ጊዜ ጀምሮ እዚህ ለምንገኝ አባላትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች አሁን በዚህ ከእኛ ጋር ለሌሉም ብዙ ወገኖቻችን ሁሉ በርካታ አገልግሎቶችን ያበረከተች ቤተክርስቲያን ናት። ብዙዎች ልጆቻቸውን ያስጠመቁባት ቅዱስ ጋብቻን የመሰረቱባት ለቅዱስ ሥጋውና ለክቡር ደሙ የበቁባት በርካቶችም ከጭንቀት ከሃዘንና ከችግራቸው የተጽናኑባት የሰማይ ደጅ ናት።

በእውነተኛው አምላካችን ደም የተመሰረተችው ይህች ቤተክርስቲያናችን የንጽህት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ቤተክርስቲያንን እምነት ሥርዓትና ትውፊት ጠብቃ ያለች በዓመት ውስጥ 365 ቀናት ክፍት ሆና በርካታ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ትሰጣለች። በኪዳን፣ በቅዳሴና በሰዓታት ጸሎታት፤ እንዲሁም በተለያዩ ክብረ በአላት፦ ለማስታወስም በአመት ውስጥ 14 ጊዜ ያህል በማኅሌት፣ ጥምቀትን ጨምሮ ዘጠኝ ጊዜ ያህል በንግሥ፣ 16 ቀን በሰሙነ ፍልሰታ፣ 6ሳምንታት በጽጌ ማኅሌት፣ 5 ቀን በሰሙነ ሕማማት እንዲሁም በመስቀል ደመራ ልዩ ዝግጅት ያላሰለሰ አገልግሎት የሚሰጠባት ታላቅ ደብር ናት።

በደብራችን የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎቶች እየተስፋፉ ከመምጣታቸው በተጨማሪ የተገልጋዩም ምእምን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመምጣቱ፤ ይበልጡንም ደግሞ በዚህ ሃገር የተወለዱ ልጆች ሃይማኖታቸውን ተምረው ቤተክርስቲያንን ለመረከብና ለማገልገል ይችሉ ዘንድ የተመቻቸ ሁኔታን ማዘጋጀት የግድ አስፈላጊ በመሆኑ በተጨማሪም ሌሎች ችግሮችን ማቃለል ይቻል ዘንድ በስፋትና በይዘት አሁን ካለንበት ቤተክርስቲያን ሰፋ ያለና ምቹ የሆነ ሁሉን የሚያሟላ አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን መስራት አማራጭ የሌለው መሆኑ ታምኖበት እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ መልካም ሥራን ለመስራት ሲነሳሱ ሁል ጊዜም ፈተና በመኖሩ ያሰብነው እቅድ ቤተክርስቲያናችን በገጠማት ፈተና ለጊዜው ተጓቶ የነበረ ቢመስልም የቤተክርስቲያናችን የአስተዳደር ቦርድ ለዚህ ታላቅ ውጥን ቅድሚያ በመስጠት በተለያዩ ጊዜያትም ከአባላት ጋር በመወያየት እና የአባላትን ይሁኝታ በማግኘት ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ሲሰራ ቆይቷል።

በእኛ በኩል ላለፈው አንድ አመት ተኩል ያህል ነገሮች አንድ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተስፋ የሚሰጡ መስለው ሲቀጠሉ ቆይተዋል። ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ፈቅዶ ይኸው ለዛሬዋ የምስራች እለት አድርሶናል።

የምሰራቹም አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ብዙ ውጣ ውረድ ያየንበት ለቤተክርስቲያን እና ለልዩ ልዩ ተቋማት መስሪያ የሚሆነውን 2.7 ኤከር ስፋት ወይንም ወደ 11 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን 2629 30th Ave S Minneapolis, 55406 ላይ የሚገኘውን ቦታ ገዝተን የቦታውን ባለቤትነት ሰነድ ከትናንት በስቲያ አርብ ጁን 17/2016 ዓ.ም ተረክበናል።

ለዚህም አባታችን መድኃኔዓለም ክብርና ምስጋና ለስሙ ይሁን እንላለን።

የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ ቤተ ክርስቲያን